የአብክመ ዋና ኦዲተር መ/ቤት የኮምቦልቻና ሸዋ ሮቢት ከተማ አስተዳደሮችን ከ2009 እስከ 2012 ዓ.ም የኦዲት ግኝቶች እርምጃ አወሳሰድ የተመለከተ ግምገማዊ ዉይይት መጋቢት 29/2014 በኮምቦልቻ ከተማ አካሔዴ!!
የከተማ አስተዳደሮቹ የ4 ዓመት የኦዲት ግኝቶች ማስተካክያ እርምጃ አወሳሰድ የግምገማ ዉይይት ላይ ከክልሉ ምክርቤት ምክትል አፈ-ጉባዔዉ አቶ አማረ ሰጤ እና የበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዋ ወ/ሮ አለምነሽ ዋጋዬ ፥ የክልሉ ከተማ ልማት ቢሮ የዓለም ባንክ የምስራቅ አማራ ቀጠና አስተባባሪ አቶ አበበ ገብረ መስቀል ፥ ከአብክመ ዋና ኦዲተር መ/ቤት ዋና ኦዲተሩን ጨምሮ የክዋኔ ኦዲት ዳሬክተር ፥ የደሴ ማዕከል የፋይናንስና ህጋዊነት ኦዲት ዳይሬክተር እና ከፍተኛ የኦዲት ባለሙያ ፥ ከሁለቱም ከተማ አስተዳደሮች ም/ከንቲባዎች ፣ ዋና አፈ-ጉባዔዎች እንዲሁም የፋይናንስና የዉስጥ ኦዲት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በዉይይቱ ተገኝተዋል፡፡
በግምገማ ዉይይቱ የከተማ አስተዳደሮቹ የ4 ዓመታት የኦዲት ግኝቶቾ ዝርዝርና የግኝቶችን ባህሪያት ያካተተ አጭር ሪፖርት በዋና ኦዲተር በኩል ቀርቦ ሰፊ ዉይይት ተደርጎበታል፡፡
በግምገማ ዉይይቱ የከተማ አስተዳደሮችን የኦዲት የግኝቶችን ባህሪያት አስመልክቶ የክልሉ ዋና ኦዲተር ሲገልጹ ዋና ኦዲተር መ/ቤቱ በየዓመቱ የከተማ አስተዳደሮቹን በተከታታይ ኦዲት እያደረገ ከችግሮቻቸው እንዲወጡ ከፍተኛ እገዛ እያደረገ ቢሆንም የከተማ አስተዳደሮቹ በኦዲት ግኝቶች ላይ እየወሰዱት ያለው እርምጃ ግን አጥጋቢ የሚባል አለመሆኑን አስታውቀዋል። የክልሉ የበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዋ በሰጡት አስተያየት የኦዲት ግኝቶች እንደ ባህሪያቸው እየተፈተሹ የማስተካከያ እርምጃ በከተማ አስተዳደሮቹ መዉሰድ እንደሚጠበቅባቸው አስታውቀዋል። በውይይቱ የማጠቃለያ አስተያየት የሰጡት የክልሉ ም/አፈ-ጉባዔ እንደገለፁት የዋና ኦዲተር መ/ቤቱ የከተማ አስተደተደሮቹ ከመገንግስትና የተለያዩ ድጋፍ ሰጭ ተቋማት በተለይም ከዓለም ባንክ ለመሠረተ ልማት ግንባታ የሚያገኙትን የበጀት ድጋፍ ለታለመለት ዓላማና ህዝብን ተጠቃሚ በሚያደርግ አካሄድ ሥራ ላይ እያዋሉ ስለመሆኑ ለማረጋገጥ በየአመቱ ከተሞቹን በኦዲት እየደገፈ እንደሚገኝ አስታውቀው የየከተማ አስተዳደሮቹ አመራርም የህዝብን ጥቅም በማስቀደምና ተጠያቂነትን በማረጋገጥ ለኦዲት ግኝቶች አፋጣኝ የእርምት አርምጃ እንዲወስዱ አሳስበው ውይይቱ ተጠናቋል፡፡


የሱፐርቪዥን ውጤታማነት የኦዲት ሥራው ጥራት መለኪያ ተደርጎ እንደሚወሰድ ተገለጸ!!
ይህ የተገለጸው የአብክመ ዋና ኦዲተር መ/ቤት የኦዲት ጥራት ማስጠበቅ ላይ ያተኮረ ግምገማዊ ዎርክ ሾፕ በባህርዳር ከተማ በአዘጋጀበት ወቅት ነው፡፡
የግምገማ ዎርክ ሾፑ የተዘጋጀበት ዋና ዓላማ በኦዲት ሥራው ሂደት በየደረጃው በሚገኙ ባለሙያዎች የሚሰጠው ሙያዊ ድጋፍና ክትትል የኦዲት ጥራትን በማስጠበቅ በኩል ያለውን አስተዋጽኦ በመገምገም ያሉበተን ድክመቶችና በሂደቱ የገጠሙትን ተግዳሮቶች ለማረምና የመፍትሔ አቅጣጫ ለመፈለግ ታሳቢ ተደርጎ ነው፡፡
በተዘጋጀው የግምገማዊ ዎርክሾፕ መድረክ ላይ ከፌደራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የክዋኔ ኦዲት ዳይሬክተር እና በፋይናንስና ህጋዊነት ኦዲት የገቢዎችና ጉሙሩክ ዘርፍ ዳይሬክተር የግምገማ ዎርክሾፑን በመምራት በአብክመ ዋና ኦዲተር መ/ቤት በኩል ደግሞ ዋና ኦዲተሩን ጨምሮ የፋይናነስና ህጋዊነት ኦዲት ማናጀሮችና ዳይሬክተሩ፣ የክዋኔ ኦዲት ማናጀሮችና ዳይሬክተሩ እንዲሁም የኦዲት ጥናት ምርምርና ስርጸት ዳይሬክቶሬት ባለሙያዎችና ዳይሬክተሩ ተሰታፊ ሆነዋል፡፡
በዚህ ግምገማዊ ዎርክሾፕ የአብክመ ዋና ኦዲተር መ/ቤት ለመስክ ቡድኖች በኦዲት ማናጀሮች የሚደረገው ሙያዊ ክትትል፣ድጋፍና ቁጥጥር እንዴት ይከናወናን? ያሉበት ድክመቶችና ተግዳሮቶችስ ምንድነናቸው? ከፌደራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ሊወስዳቸው የሚችሉ ተሞክሮዎች ምን ምን ናቸው? የሚሉት ጉዳዮች በዝርዝር ተነስተው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
በግምገማ ዎርክሾፑ ማጠቃልያም በማናጀሮች ለመስክ ቦድኖች የሚሰጠው ሙያዊ ድጋፍና ክትትሉ ለኦዲት ጥራት የሚጠበቅብትን አስተዋፆ እንዳያደርግ ማነቆ የሆኑ ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች በአጭር ጊዜ የመፍትሔ አቅጠጫ እንዲሰጣቸው የጋራ መግባባት ላይ ተደርሶ የግምገማ ዎርክ ሾፑ ተጠናቋል፡፡


የአብክመ ዋና ኦዲተር መ/ቤት የ7 ከተማ አስተዳደሮች የ5 ዓመታትን የኦዲት ግኝት እርምጃ አወሳሰድ በተመለከተ ከየከተሞቹ አመራሮች ጋር የግምገማ ውይይት አካሔደ!!
የግምገማ ውይይቱ ዋና ዓላማ ያደረገው የከተማ አስተዳደሮቹ ከ2009 እስከ 2013 ዓ.ም በአብክመ ዋና ኦዲተር መ/ቤት የኦዲት ግኝቶች ላይ እየወሰዱት ያለውን የማስተካክያ እርምጃና ከዓመት ዓመት የተገኙ ለውጦችን ከሚመለከታቸው አመራሮችና ባለሙያዎች ጋር መገምገም ነው፡፡
በአብክመ ዋና ኦዲተር መ/ቤት የ5 ዓመት የኦዲት ግኝት እርምጃ አወሳሰዳቸው የግምገማ ውይይት የተደረገባቸው የከተማ አስተዳደሮች ደብረ ብርሃን፤ደብረታቦር፤ፍኖተ ሰላም፤ጎንደር፤ ደባርቅና አይከል ከተሞች ናቸው፡፡
በሁሉም የግምገማ መድረኮች የከተማ አስተዳደሮቹ የ5 ዓመታት የኦዲት ግኝቶች በዝርዝር እና የግኝቶችን ባህሪያት የሚያሳይ አጭር ሪፖርት በዋና ኦዲተር ባለሙዎች እየቀረበ ሰፊ ዉይይት ተደርጎበታል፡፡
በ7ቱም የውይይት ማጠቃለያዎች ላይ የከተማ አስተዳሮቹ አመራር የኦዲት ግኝቶች አርምጃ አወሳሰድ ላይ ትኩረት ሰጥቶ በቅንጅት ሊሠራ እንደሚገባው በዋና ኦዲተር መ/ቤቱ በኩል ማሳሰቢያ የተሰጠ ሲሆን ከተሞቻቸውን ወክለው በየግምገማ መድረኮቹ የተሳተፉ የአመራር አባላትና ባለሙያዎች በሰጡት አስተያየት የግምገማ መድረኩ ትልቅ ትምህርት ያገኙበት መሆኑን ገልጸው ከችግሩ በዘላቂነት ለመውጣት ያለፉት ዓመታትን የኦዲት ግኝቶች በጥልቅት ከሁሉም የሴክተር አመራሮች ጋር በመገምገም በየሴክተሩ የሚከሰቱ የአሠራር ግድፈቶችና የህግ ጥሰቶችን ቀድሞ የመከላለከልና ግኝቶች እንዳይከሰቱ ቀድሞ ለመከላከል የሚስችላቸው ቅንጅታዊ አሠራር እንደሚዘረጉ ገልጸው የግምገማ ውይይቱ ተጠናቋል፡፡

